[Unicode]   ዩኒኮድ ምንድን ነው? Home | Site Map | Search
 

ዩኒኮድ ምንድን ነው?

ዩኒኮድ ለእያንዳንዱ ፊደል፣
ማንኛውም ዓይነት ኮምፒውተር ቢሆን፣
ማንኛውም ዓይነት ፕሮግራም ቢሆን፣
ማንኛውም ዓይነት ቋንቋ ቢሆን፣
ልዩ የሆነ ቍጥር ያዘጋጃል።

በመሠረቱ ኮምፖውተሮች የሚሠሩት ከቍጥሮች ጋር ነው። ለእያንዳንዱ ፊደል ቍጥሮችን በመመዝገብ ፊደሎችንና ሌሎች አሃዞችን ይመድባሉ። ዩኒኮድ ከመፈልሰፉ በፊት እነዚህን ቍጥሮች ለመሰየም በመቶ የሚቆጠሩ የተለያዩ የስያሜ አፈታት ዘዴዎች ነበሩ። ይህም ማለት አንድ የተወሠነን ስያሜን ለመፍታት ብዙ አሃዞችን ያካተተ አልነበረም። ለምሳሌ የአውሮፓ ኅብረትን ብንወስድ ሁሉንም ቋንቋዎቹን ለመሸፈን ብዙና የተለያዩ የአፈታት ዘዴዎች ያስፈልግ ነበር። ለእንግሊዘኛ ቋንቋ እንኳን አንድ ብቸኛ የአፈታት ዘዴ ለሁሉም ፊደሎች፣ ሥርዓተ ነጥቦችና ምልክቶች በጋራ ለመጠቀም በቂ አልነበረም።

እነዚህ የስያሜ አፈታት ዘዴዎች እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑበትም ጊዜ አለ። ይህም የሚሆነው ሁለት የአፈታት ዘዴዎች ለተለያዩ ፊደላት አንድ ዓይነት ቍጥር በሚጠቀሙበት ጊዜ ወይንም ደግሞ የተለያዩ ቍጥሮችን ለአንድ ፊደል በሚጠቀሙበት ጊዜ ነው። ማንኛውም ኮምፒውተር በተለይ አስተናጋጆች የተለያዩና ብዙየአፈታት ዘዴዎችን መደገፍ ያስፈልጋቸዋል። ግን በተለያዩ የአፈታት ዘዴዎች ወይም ኮምፒውተሮች መሀል መረጃ በሚተላለፍበት በማንኛውም ጊዜ የመዘበራረቅ አደጋ ሊከሰት ይችላል።

ዩኒኮድ ይህን ሁሉ ለውጦታል

ዩኒኮድ ለማንኛውም ኮምፒውተር፣ ለማንኛውም ፕሮግራምና ለማንኛውም ቋንቋ ለእያንዳንዱ ፊደልተፈላጊውን ልዩ የሆነ ቍጥር ያቀርባል። የዩኒኮድን የአሠራር ዘዴ በአሁኑ ጊዜ በታወቁት ታላላቅ መሪ ኢንዱስትሪዎች እንደ Apple, HP, IBM, JustSystem, Microsoft, Oracle, SAP, SUN, Sybase, Unisys, እና በሌሎችም ዘንድ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ዩኒኮድ እንደ XML, Java, ECMAScript (JavaScript), LDAP, CORBA 3.0, WML, ወዘተ ባሉ ወቅታዊ ደረጃቸውን በሚጠብቁ ዘንድ ተፈላጊነት ያለው ሲሆን ISO/IEC 10646ን በሕጋዊ መልኩ ጥቅም ላይ የሚያውልበት ነው። ዩኒኮድ በብዙ የኮምፒውተር መምሪያ ፕሮግራሞች፣ ማንኛቸውም አዳዲስ የድረገጽ መመልከቻ ፕሮግራሞች እና እንዲሁም የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚደግፉት ነው። ዩኒኮድ በተለያዩ የአሠራር ዘዬዎች፣ ተጨማሪ ፕሮግራሞች፣ ድረገጾች እና በሌሎችም ምርቶች የተደገፈ ነው። የዩኒኮድ ስታንዳርድ ብቅ ማለቱ እና ለሱ ድጋፍ የሚሰጡ መሣሪያዎች መቅረባቸው በዘመኑ ከተፈጠሩት አለማቀፋዊ የሶፍትዌር የቴክኖሎጂ ክስተቶች ዋናዎቹ ናቸው።

ዩኒኮድ በኔትወርክ በሚሰሩ ኮምፒውተሮች እና ድረገጾች ጋር በማቀናጀት በዋጋ በኩል ታላቅ የወጪ ቅናሽ ይሰጣል። አንድን የሶፍትዌር ምርት ወይንም አንድን ድረገጽ ለተግባረ ብዙ ኮምፒውተሮች፣ ቋንቋዎችና ሀገሮች እንደገና ማስተካከል ሳያስፈልግ ተግባር ላይ ማዋል ይችላል። መረጃዎቹን ምንም እንከን ሳያጋጥማቸው በልዩ ልዩ የአሠራር ዘዴዎች እንዲንሸራሸሩ ያደርጋል።

የዩኒኮድ ጉባኤ

የዩኒኮድ ጉባኤ አትራፊ ድርጅት ሳይሆን የተመሠረተው የዩኒኮድን ደረጃ ለማሣደግ፣ ለማስፋፋት እና በተግባር ላይ እንዲውል ለማድረግ ነው። ዩኒኮድ የፅሑፍን አቀራረብ በወቅታዊ ሶፍትዌር ውጤቶችና ደረጃዎች ይደነግጋል። የጉባኤው አባልነት ሰፋ ያለ የኮምፒውተርና ከኮምፒውተር ጋር ተቀናብረው የሚሄዱ ድር ጊቶችን የሚሸፍን ትላልቅ ድርጅቶችን ያካተተ ነው። ይህ ማዕከል የሚደገፈው ከአባሎቹ በሚዋጣው ገቢ ብቻነው። በአለም ዙሪያ ላሉ የዩኒኮድን ስታንዳርድ (ደረጃ) ለሚደግፉ እና በእድገቱም ሆነ በአሠራሩ ለመርዳት ለሚፈልጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የዩኒኮድ ጉባኤ አባልነት በር ክፍት ነው።

ለተጨማሪ መረጃ ማውጫውን ቴክኒካዊ መግቢያ እና ጠቃሚ ምርቶችን ይመልከቱ

 

Amharic translation by The Ge'ez Frontier Foundation